scientheology

ከተፈጥሮአችን እንማር 
በዚህ ሥዕላዊ መግለጫ የሚታየው በሰውነታችን ውስጥ በእያንዳንዷ ከጤፍ ሺህ ጊዜ በምታንሰዋ ህዋስ (cell) የሚከናወን የሃይል ማመንጫ ውስብስብ ሂደት ነው (cellular  respiration) ። የተመገብነው ምግብ  በያንዳንዱ ህዋስ ውስጥ በዚህ መልኩ ነው የሃይል ምንጭ የሚሆነው። ይህ እንግዲህ  በሁሉም ህዋሳታችን ከሚከናወኑት የተለያዩ  ሂደቶች (processes) መካከል አንዱ ነው። ይህን የመሳሰሉ ሌሎች ብዙ የተለያዩ ሥርዓቶች ከጤፍ ብዙ ጊዜ  ያህል በምታንሰዋ ሕዋስ ውስጥ በየእለቱ ይካሄዳሉ። አሉ ከተባሉ ታላላቅ ፋብሪካዎችና ማምረቻዎች ይልቅ ውስብስብ ነው
  ከሁሉ የሚገርመው ግን በዚህ ውስብስብ ሂደት ብዙ ሰራተኞች(organells)  ኤንዛይሞች(enzymes) መልእክቶች(signals)  እርከኖችና መንገዶች(steps and  pathways) ተሳታፊ ናቸው። ታዲያ አንዱ የሌላውን ትእዛዝ እየተቀበለ፥ በሚገባው መንገድ እየሄደ፥ ሰዓቱን ጊዜውን ሳያዛባ እየሰራ የሰውነታችን ደሀንነት  በየእለቱ እየጠበቀ ይኖራል። በድንገት አንዱ ሰራተኛ፥ ኤንዛይም፣መልእከት፥ ጊዜው ወይንም መንገዱ ከተሳሳተ ቀላል የማይባል የጤና ችግር ያስከትላል። ስኳርን የመሳሰለሉ መፈወሻ የሌላቸው ህመሞች ይከሰታሉ። 


                      ይህን ቅንጅት፥ ሥርዓትና ኅብረት ከሕዋሳት ጀመሮ መላው ሰውነታችን ይፈጽሙታል። ሳንባ፥ ጨጓራ፥ ጉበት፥ ኩላሊት፥ አንጎል፥ እንዲሁም ደማችን በመስማማትና በመተባበር በመከባበር ሥራቸውን እየሰሩ ጤነኛ  ሰው ሆነን እንድንኖር ያደርጉናል። አንዱ አልታዘዝም ካለ ትልቅ የጤና ቀውስ ያስከትላል። ለምሳሌ ነጭ የደም ህዋሳት መከላከል ከሚገባቸው በሽታ አልፈው ያልታዘዙትን ነገር እንከላከላለን ሲሉ እንደ አስምና አለርጂ (asthma and alergies) የመሳሰሉ ህመሞች ይከሰታሉ።  በጣም የሚገርመው ነገር ሰው በተለያዩ የበሽታ አምጪ ተውሳክ ( bacteria, protozoa, worms) የተነሳ ቢታመም መድኃኒት ወስዶ ፈጽሞ ሊድን ይችላል።  ነገር ግን ከሰውነታችን ህዋሳት ወይ  ኤንዛይሞች ወይንም ሆርሞኖች ከስርዓት ውጪ መሆን የተነሳ  የሚመጣ በሽታን ግን ማዳን አይቻልም በቀረን ዘመን የማስታገሻ ወይንም የመተኪያ መድኀኒት እየወሰድን መኖር ነው።  ደሃ  ሀገሮች መድሃኒት ባላቸው የተውሳክ በሽታዎች ሲቸገሩ ሃብታም ሃገሮች ደግሞ ፈውስ በሌላቸው ከራስ ሰውነት በሚነሱ ህመሞች ይሰቃያሉ። ልዩነቱ አይገርምም።

     
   ወይ የእግዚአብሄር ጥበብ
 
       እግዚአብሄር አንድነት መስማማትን መደማመጥን በአይን በማይታዩ ህዋሳትም ሆነ በሚታዩ ብልቶቻችን ላይ ሰርቶ ድንቅ  ምሳሌውን ትቶልን ነበር።                  ፩ቆሮ 12፥14-7
               " አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና። እግር እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፥ ይህን  በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን?  ጆሮም እኔ ዓይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ቢል፥ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን?  አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል። ሁሉም አንድ ብልት ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ? ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው።  ዓይን እጅን። አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን። አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤  ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤  ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው።  አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።  እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ"። 
       ታዲያ  ይህን እንዳናስተውል ማን አዚም አደረገብን። ምነው መስማማት መከባበር መደማመጥ መታዘዝ አቃተን? በዚህ ችግር ምክንያት ብዙ ፈውስ ያጡ በሽታዎች በመካከላችን ገብተዋል። ከውጪ የሚነሱብን ችግሮች በጀግንነት በተጋድሎ እንዳባቶቻችን ልናሸንፍ እንችላለን። ከራሳችን መካከል ግን የመጡ ችግሮችን  እንዴት እንፍታቸው?  ከላይ እንደተገለጸው ከባድ ነው። 
     እሱ ትንሽ ነው፥ ያልተማረ ነው ፥ ደሃ ነው፥ ቀይ ነው ጥቁር ነው፥ ኦሮሞ ነው አማራ ነው ጉራጌ ነው ትግሬ ነው፥ አሪፍ ነው ፋራ ነው እያልን ብንለያይ ባንደማመጥ ባንከባበር ትርፉ ፈውስ በሌለው በሽታ እንደሚሰቃይ ሰውነት ያለ ኅብረተሰብ መሆን ነው።  
    ስለዚህ ከህዋሳቶቻችንና ከብልቶቻችን ምሳሌውን እንማር። እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ይናገራል ካስተዋልነው ምሳሌውን በራሳችን በውስጣችን ትቶልናልና እንማር። መከባበር መስማማትን መደማመጥን አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ መባባልን ገንዘብ  እናድርግ።  
                      ከራሳችን ተምረን እንድለወጥ ማስተዋል ይስጠን